ለማይቀረው ለውጥ እንዘጋጅ

images (3)

 

 ከአቡ ሀጋር 

ሙስሊሙ ማህበረሰብ ከዘጠኝ ወራት ቀደም ብሎ የጀመረውን የኃይማኖት ነጻነትን የማስከበር ትግሉን መሪዎቹ ከታሠሩም በኃላ እንኳን ቢሆን ታላቅ ትእግስትና ጥበብ በተሞላበት ሁኔታ ቀጥሏል። ተቃውሞው አርብ ኦገስት 17 እንደተለመደው በአንዋር መስጊጅ በከፍተኛ ድምቀት ተከናውኗል፤ ምንም እንኳን የተቃውሞው መገለጫ በአይነቱ ለየት ያለ ቢሆንም። ሙስሊሙ የአርብ ኦገስት 17 ተቃውሞውን ያሳየው እንደ ወትሮው የአንዋርን አካባቢ በመቶ ሺህዎች በሚቆጠሩ ምእመናኑ በማጥለቅለቅ ሳይሆን መስጂዱን ባዶ በማድረግ ነበር። ይህም የሙስሊሙ አንድነትና በአሚሮቹ ትእዛዝ ሥር ሆኖ መብቱን ለማስከበር ቆርጦ መነሳቱን በድጋሚ ያረጋገጠበት ታላቅ ትእይንት ነበር፤ አላህ ወክበር ወሊላሂል ሃምድ!

በሙስሊም ዜጎች ላይ ሸርን ስታውጠነጥን የኖረችው የጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ አእምሮ በአላህ ፈቃድ ምህዋሯን ከመሳቷ ጋር በተያያዘ ብቻ ሳይሆን ቀደም ብሎም በሙስናና አምባገነን አስተሳሰብ በወለዳቸው የእርስ በርስ መቃቃሮች ብል እንደበላው ግንድ ቀፎውን የቀረው ኢህአዴግ የአገልግሎት እድሜውን ጨርሶ ለሌላ ለማስረከብ መንገድ ላይ ይገኛል። ታዲያ በዚህ የለውጥ ወቅት አንዱ አምባገነን ሄዶ በሌላ አምባገነን እንዳይተካ፣ አንዱ ጸረ ኢስላም ኃይል ተወግዶ በሌላ ጸረ ኢስላም ኃይል እንዳይተካ ኢትዮጵያውያን በሙሉ በጥቅሉ፣ ሙስሊሞች ደግሞ በተለይ የለውጡን ሂደት በከፍተኛ ንቃት መከታተል ብቻ ሳይሆን ለውጡ ሊይዘው በሚገባ መልክ ዘሪያም ንቁ ተሳትፎ ሊያደርጉ ይገባል።

ኢህአዴግ የሥልጣን ዘመኑን ለማራዘም በማሰብ ላለፉት 21 ዓመታት በኢትዮጵያ ህዝብ ላይ ከፍተኛ ወንጀሎችን ፈጽሟል። ህዝቦች በመካከላቸው ያሉትን የብሄር፣ የኃይማኖትና የመሳሰሉ ልዩነቶች እንደያዙ ተቀራርበው፣ ተማምነውና ተከባብረው የጋራ ሀገራቸውን ለማበልጸግ እንዲሰሩ ለማድረግ ከመሞከር ይልቅ በመካከላቸው ያሉት ልዩነቶች ይበልጡኑ እንዲሰፉና እንዲጠናከሩ በማድረግ የሀገሪቱን ህልውና ከመቸውም ጊዜ በበለጠ አደጋ ላይ ጥሏል።

ኢህአዴግ ያቀደው ተሳክቶለት ቢሆን ኖሮ ይሄኔ ሙስሊሙና ክርስቲያኑ በቡድን ተከፋፍሎ በተጨፋጨፈ ነበር። ነገር ግን አላህ ሱብሃነሁ ወተዓላ የቅን አማኞቹን ዱዓ ይሰማልና እነሆ ጥፋትን የጠነሰሰች አእምሮ በክፋቷ ታስራለች። አላህ ወአክበር ወሊላሂል ሃምድ!

አላህ ሱብሃነሁ ወተዓላ የኢስላም ጠላቶች እስልምናን ለማጥፋት ይሸርባሉ ነገር ግን አላህ ሸራቸውን ይመልስባቸዋል በማለት ቅዱስ ቁርአኑ ላይ ባሠፈረው ቃል መሰረት እነሆ ሙስሊሙን እርስ በርሱና ሙስሊሙን ከህዝበ ክርስቲያኑ ጋር ለማጋጨት ታቅዶ የተሸረበው ሴራ እነሆ ለሙስሊሙ አንድነት መጠናከ፣ እነሆ ለሙስሊሙና ለክርስቲያኑ መቀራረብ ምክንያት ሊሆን ችሏል፤ አላህ ወአክበር ወሊላሂል ሃምድ!

በአሁኑ ሰዓት የተፈጠረውና ከቀን ወደ ቀን እየተጠናከረ በመሄድ ላይ የሚገኘው የሙስሊሙ አንድነት ለሙስሊሙ መብት በዘላቂነት መከበር ዋነኛው መሳሪያ እንደሚሆን ምንም ጥርጥር የለውም። ስለዚህ ለሙስሊሙ አንድነት መጠናከር መስራት የሁሉም ሙስሊም ኃይማኖታዊ ግዴታ ነው ለማለት ይቻላል። ሙስሊሙ ማህበረሰብ አሁን በስልጣን ላይ ባለው የኢህ አዴግ መንግስትም ሆነ ቀደም ባሉት የደርግና የአጼው ስርአቶች ጭቆናን ሲያስተናግድ ብቻ ሳይሆን ጭቆናውንም በተለያዩ መንገዶች ሲታገል ቆይቷል። በአጼው ዘመን ሙስሊሞች በተናጥልና በህብረት ባደረጓቸው ተጋድሎዎች አንዳንድ ከፍተኛ ድሎችን አስመዝግበዋል። ቀደምት የሙስሊሙ ትግል ካስመዘገባቸውም ድሎች መካከል የአለሙ የሙስሊሞች ማህበር አጼው በሙስሊም ዜጎቹ ላይ በሚፈጽማቸው ጭቆናዎች ሳቢያ ከአንዴም ሁለቴ እንዲወገዝ ማድረጋቸው ይገኝበታል። በ1974 በአውሮቻውያን አቆጣጠር ሙስሊሞች ያደረጉት ታላቅ ሠላማዊ ሠልፍም ለአጼው መንግስት መገርሰስ የራሱን አወንታዊ ሚና መጫወቱ የሚካድ አይደለም። ሙስሊሞች ጨቋኙ ወታደራዊ የደርግ መንግስት እንዲንኮታኮትም እንዲሁ እንድ ቡድንም ባይሆን እንደ ዜጋ በተለያዩ እንደ ኢህአፓና ወያኔን በመሳሰሉ የተቃውሞ ድርጅቶች ውስጥ በመሳተፍ ከፍተኛ መስዋእትነትን ከፍለዋል። ያም ሆኖ ግን መብታቸው እስከአሁንም ድረስ በተረጋገጠበት ሁኔታ ላይ ይገኛሉ። እርግጥ ነው አንድ ስርዓት ተወግዶ በሌላኛው ስር ዓት ሲተካ የሙስሊሙን ድጋፍ ለማግኘት ሲባል አንዳንድ አወንታዊ ለውጦች ታይተዋል። ነገር ግን በተደጋጋሚ የታየው ሌላው ነገር መንግስታቱ ጥቂት ከተረጋጉ በኃላ ህግን በጣሰ መልኩ የሙስሊሙን መብት ቀስ በቀስ በመሸርሸር ወደ ቀድሞው ፍጹም የጭቆና መስመር ውስጥ መመለሳቸው ነው።

ይህንን ጉዳይ ሙስሊሙ በሚገባ ትኩረት ሰጥቶ ሊዘጋጅበት የሚገባ ነው የሚል እምነት አለኝ። መብት የሚወሰድ እንጂ የሚሰጥ አይደለም። ስለዚህ ሙስሊሙ ሁሌም እንዲሰጠው የሚጠይቅ አካል እንጂ የመብቱ አስከባሪ ሳይሆን የኖረበት ዘመን ማብቂያው አሁን እንዲሆን ከተፈለገ ሙስሊሙ ይህንን ግቡ አድርጎ መንቀሳቀስ ይኖርበታል። ኢትዮጵያ የሙስሊሙም የክርስቲያኑም፣ የአማኙም ያላማኙም የጋራ ሀገር ናት። ስለዚህም ህዝቦቿ በሙሉ እዳዋንም ሆነ ትርፏን ያለምንም ማበላለጥ በእኩል ሊካፈሉ ይገባል። ስለዚህም በማህበረሰቡ የተለያዩ ወገኖች መካከል፤ በተለይም በታላላቆቹ የሙስሊምና ክርስቲያን ሁለት ማህበረሰባት መካከል ሊኖር የሚገባው የግንኙነት መሰረት የመወዳደርና የመፎካከር፣ የጥርጣሬና የጥላቻ ስሜት ሳይሆን የመተባበርና የመረዳዳት፣ የመተማመንና የመከባበር ነው። ስለዚህም በአሁኑ ሰዓት እየተፈጠረ ያለው መቀራረብ ይበልጡኑ እንዲጠነክር ሙስሊሙ ሆነ ክርስቲያኑ ወገን የበኩላቸውን ማድረግ ይኖርባቸዋል።

ይህችንን የጋራ ሀገራችንን መምራትና ማስተዳደር የአንዱ ብቻ ሳይሆን የሁሉሙ ማህበረሰብ መብትና ግዴታ እንደመሆኑ መጠን በሀገሪቱ በሚገኙ የተለያዩ የማህበረሰብ አባላት መካከል የተሻለ ግንኙነትን መፍጠር አማራጭ የሌለው መሆኑን ሁሉም ወገን ሊረዳውና በጸጋም ሊቀበለው የሚገባ ጉዳይ ነው።

ሙስሊሙ ማህበረሰብ ከዚህ ቀደም ሲደረግ እንደኖረው ሁሉ ለትግሉ መስዋእትነትን ከከፈለ በኃላ ከድል አጥቢያ መብቱ እንዳይሸረሸር ከፍተኛ ንቃትና ጥንቃቄ ሊያደርግ ይገባል። ለዚህም ተግባር አንዱና ዋነኛው ነጥብ አንድነቱን ማጠናከር ነው። እንደ ከዚህ ቀደሙ ሁሉ ሙስሊሙ መብቱን ጠያቂ ሆኖ እንዳይቀጥል ከተፈለገ ሙስሊሙ በተናጥል የሚያደርጋቸው እንቅስቃሴዎች እንደተጠበቁ ሆነው በቡድንም መንቀሳቀስ መቻል ይኖርባቸዋል። አሁን ያለንበት ወቅት የለውጥ እንደመሆኑ መጠን ሙስሊሙ ማህበረሰብ እንደ አንድ የሀገሪቱ ጉዳይ የሚመለከተው አካል ለኢትዮጰያ ያለውን ራዕይ ሰንቆ ወደ ኢትዮጵያ የፖለቲካ መድረክ መምጣት ይኖርበታል እላለሁ። አላሁ ዓለም!

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *