About us

የራዲዮ ነጋሺ ዓላማና ግብ 

ቢስሚላሂ አረህማን አረሂም

አሰላሙ አለይኩም ወራህመቱላሂ ወበረካቱ

ራዲዮ ነጋሺ የተቋቋመው ማርች 9 2005 እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር ነው። የራዲዮ ነጋሺ አመሰራረት የራሱ የሆነ ታሪክ አለው። የራዲዮ ጣቢያው ባለቤት የነበረው ነጃሺ የኢትዮጵያውያን ሙስሊሞች ማህበር በስዊደን ሬዲዮ ጣቢያውን ከመክፈቱ በፊት ለአባላቱ የሚያደርጋቸው ጥሪዎች ሲኖሩት በወቅቱ ስቶክሆልም ከተማ ውስጥ በነበሩ ሁለት (አንደኛው የመንግስት ደጋፊ አንደኛው ደግሞ ተቃዋሚ በሆኑ) ”ኢትዮጵያዊ ” የራዲዮ ጣቢያዎች ይጠቀም ነበር። ነገር ግን ይህ ሁኔታ የሚያዛልቅ አልሆነም።

የመንግስት ተቃዋሚ የሆነው የሬዲዩ ጣቢያ ”የመንግስት ደጋፊ የሆነውን ጣቢያ ትታችሁ ከእኛ ጋር ብቻ መሆን አለባችሁ” የሚል ቅድመ ሁኔታ ሲያስቀምጥብን፣ የመንግስት ደጋፊ የሆነው ”ሠላም” በመባል የሚታወቀው ራዲዮ ጣቢያ ደግሞ (ለሙስሊሞች ያለውን ቀና ያልሆነ አመለካከት አላህ ሲያጋልጥበትና እኛን ደግም ከእንቅልፋችን ሲያነቃን) በአመት ውስጥ ሦስቴና አራቴ የሚያስተላልፍልን ማስታወቂያ በዝቶበት አንድ ቀን የራዲዮ ፕሮግራም አዘጋጁ ማይክሮፎኑ የተዘጋ መስሎ ”እነዚህ እስላሞች አላበዙትም እንዴ ….. ” እያለ ሲመነጫጨቅ ሁላችንም ለመስማት በመቻላችን እስከመቼ ድረስ ነው የማንም ማላገጫ ሆነን የምንኖረው? ለምን የራሳችንን ጣቢያ አንከፍትም የሚል ሃሳብ መጣብንና ምንም እንኳን ልምድ ያለው ሰው ከመካከላችን ባይኖርም በሂደት እንማራለን በማለት ራዲዮ ነጃሺን በመስከረም 2005 ልናቋቁመው በቃን።  

ለራዲዮ ነጃሺ መመስረት ይሄ ከላይ የጠቀስነው ምክንያት እንደ ማቀጣጠያ ሆነን እንጂ ሃሳቡ ፈጽሞ አልነበረንም ማለት አይደለም። ቀደም ብሎም ቢሆን ከአባላቶቻችን ጋር ሃሳብ የምንለዋወጥበትና ብሎም የምንማማርበት መድረክ እንደሚያስፈልገን ይሰማን ነበር። ከዚሁ አላማ በመነሳትም ወርሃዊ መጽሄት እስከመጀመር ደርሰን ነበር፤ ነገር ግን አብዛኞቹ የማህበራችን አባላት ከማንበብ ይልቅ ማዳመጥን እንደሚመርጡ ከተረዳን በኃላ በድምጽ ልንገናኝ የምንችልበትን መንገድ ስናሰላስል ስለነበረ ይህ ቀደም ብሎ የጠቀስነው አጋጣሚ ውሳኔያችንን አፋጠነው ለማለት ይቻል ይሆናል እንጂ አጋጣሚው ባይፈጠር ኖሮ ራዲዩ ነጋሺ እስከ አሁንም ባልተመሰረተ ነበር ብሎ ለመናገር አይቻልም። ምክንያቱም የሙስሊሙን የህሊና ንቃት ለማዳበርና በጋራ ለአንድ አላማ እንዲነሳ ለማድረግ ሚዲያ የሚሰጠውን ጥቅም ብዙዎቻችን እየተረዳን የመጣንበት ወቅት ላይ ደርሰን ነበርና ነው። በምእራቡ አለም በሚገኙ የተለያዩ ሃገራትና በኢንተርኔት  በኢትዮጵያዊነት ስም የሚንቀሳቀሱ በርካታ ሚዲያዎች ቢኖሩም መድረኮቹ በአብዛኛው የተያዙት ኢትዮጵያዊ የሚለውን ጽንሠ ሃሳብ ባልተረዱ ወይንም አውቀው በተኙና የዝሆን ጆሮ የሰጎን አእምሮ ይስጠኝ ባሉ ጠባብ አመለካከት ባላቸው ግለሰቦች በመሆኑ የኢትዮጵያዊው ሙስሊም ድምጽ በእነዚህ ሚዲያዎች ላይ መድረክ ተነፍጎትና ድምጹ ታፍኖ በመቆየቱ እያለ እንደሌለ እንዲቆጠር፣ ብሶቱ በአደባባይ ወጥቶ እንዳይሰማና ለመብቱ የሚያደርገውም ትግል የጋን ውስጥ መብራት ሆኖ እንዲቀር ምክንያት ሊሆን ችሏል። ሙስሊሙን የሚመለከቱ ዜናዎችና ድርጊቶች ለመድረክ እንዳይበቁ በሚጣልባቸው ማእቀባት ሳቢያ መቀሌ ወይንም ጎንደር ላይ የደረሰ ጭፍጨፋ ለአዲስ አበባ ሰው እንግዳ እንደነበረና እስከአሁንም ድረስ ይህ ችግር ገና እንዳልተፈታ ሁሉም የሚያውቀው ነው። ይሄ ደግሞ ተበዳዮች ረዳት እንዳያገኙ በዳዮችም በሚፈጽሟቸው ግፎች እንዲቀጥሉ ዋና ምክንያት ከሆኑት አንዱ እንደሆነ ይታወቃል። ሙስሊሙ ኢትዮጵያዊ ላይ በሚደረጉት የአፈና እርምጃዎች የተነሳ ሙስሊሙ አንድ የጋራ መድረክ ፈጥሮ ሃሳቡን እንዳያንሸራሽርና አልፎም በጋራ በተስማማባቸው ጉዳዮች ዙሪያ በመሰባሰብ በአንድነት መብቱን ለማስከበር እንዳይንቀሳቀስ እንቅፋት እንደሆነውም ግልጽ ነው። የሃገራችን ታሪክ የተዛባና ሁሉን አቀፍ አለመሆኑን ብዙ ሰው የሚስማማበት ቢሆንም ይህንን ለመቀየርና ታሪካችን ሁሉን አቀፍ እንዲሆን ለማድረግ የሚያስፈልገውን መድረክም ሳያገኝ ቆይቷል። እነዚህ እንግዲህ የሚዲያ አለመኖር ከፈጠራቸው ችግሮች መካከል ከብዙው በጥቂቱ የሚጠቀሱ ናቸው። እንግዲህ ራዲዮ ነጋሺ የተመሰረተው ለእነዚህ ከላይ ለጠቀስናቸው ችግሮች አቅም በፈቀደ መጠን መፍትሄ ለመሆን በማሰብ ነው። እነኝህን ከላይ የጠቀስናቸውን አላማዎች ይዞ የተነሳው ራዲዮ ነጃሺ ከተመሰረተ ጊዜ አንስቶ በደአዋ፣ በታሪክና በተለያዩ ኢትዮጵያውያን ሙስሊሞችን በሚመለከቱ ማህበረሰባዊ ጉዳዮች ዙሪያ ፕሮግራሞችን እየሰራ ለአድማጮቹ በማቅረብ ግልጋሎት በመስጠት ላይ ይገኛል። የአላህ ፈቃድ ከሆነ ለወደፊቱም ቢሆን እቅዱ የፕሮግራሞቹን ይዘትና ጥራት እያሻሻለ ለመቀጠል እንደሆነ በዚሁ አጋጣሚ ለአድማጮቹ ለመግለጽ ይወዳል።  የኢትዮጵያን ሁኔታ ቀረብ ብሎ ለተመለከተ የሙስሊሙ ችግር ወይንም ሙስሊሙ ላይ የተደረገውና እየተደረገም ያለው የተቀነባበረ አፈና ዘርፈ ብዙ መሆኑን በቀላሉ ሊገነዘብ ይችላል። ሙስሊሙ በታሪክ ተራኪያን ብቻ ሳይሆን በተለያዩ የህብረተሰብ በግለጫ የሥነ ጥበብ ሥራዎችም ውስጥ ያለው ተሳታፊነት ከመንደር ባለ ሱቅነት ያላለፈ በመሆኑ እያለ እንደሌለውና የባይተዋርነት ስሜት እንዲያድርበት ሌላ ተጨማሪ ምክንያት ሆኗል። ሙስሊሙ ሌሎች የሚሰጡትን ሚና አሜን ብሎ ተቀብሎ የመኖሩ ሁኔታ ከአሁን በኃላ መቀጠል የለበትም። ሙስሊሙ ራሱ የራሱን ሥነ ህይወት፣ የኑሮ ገጠመኞችና ልምዶች መግለጽ መቻል አለበት። ራዲዮ ነጃሺ ከዚህ እምነት በመነሳት የሙስሊሙን የዕለት ተዕለት ህይወት ከተለያዩ አቅጣጫዎች የሚገልጽ የተለያዩ የስነ_ጥበብ ስራዎች ለህዝብ እንዲቀርቡ ማበረታታት ይፈልጋል። ስለሆነም ክቡራን አድማጮቻችንና የድህረ ገጾቻችን ደንበኞች የሉዋችሁን እንደ ግጥሞች፣ ልብ ወለድ ትረካዎች፣ ተረትና ምሳሌዎች፣ የተለያዩ ሙስሊም ግለስቦች ገድሎች፣ ታሪኮችና የመሳሰሉ የሥነ_ጥበብ ሥራዎች ወደ እዚህ በአዲስ መልኩ ባዋቀርነው ድህረ ገጾቻችን በመላክ ለህዝብ እይታ እንድታቀርቡ እንጋብዛለን። የዚህ መድረክ አላማ እስላማዊ ደዓዋ ከመስጠት በተጨማሪ የሙስሊሙን የእለት ከእለት አኗኗር ለማሳየትና በተለይም በሂደት የሥነ ጽሁፍ ጥበብን ማዳበር የሚቻልበትን መንገድ ለመክፈት ስለሆነ በተለይ በዚህ ረገድ ፍላጎት ያላችሁ ሁሉ ይህንን መድረክ እንድትጠቀሙበት እናሳስባችኃለን።  ኢትዮጵያዊው ሙስሊም ላይ የተጣለበትን ከሃገሩ የማግለል እርምጃ ማሸነፍ የሚቻለው በማማረርና ተቃውሞን በማሰማት ብቻ ሳይሆን በሃገሩ ጉዳይ ላይ በቀጥታ ተሳታፊ በመሆን ነው። የገዛ ሃገራችንን ሌሎች ሲገልጿት እኛን ለምን አገለሉን ብለን ከማማረር ይልቅ ራሳችንን በተለያዩ መንገዶች መግለጽና መተንተን መቻል አለብን። እኛ የቤት ሥራችንን መስራት ስንጀምር ብቻ ነው ሌሎችም የሥራዎቻቸውን ጎዶሎነት የሚረዱት። ስለዚህ የቤት ሥራችንን ለመስራት የሚያስፈልገውን ጊዜ እንስጥ እያልን ሥራችን የተሳከ ይሆን ዘንድ አላህ ሱብሃነሁ ወተአላን እንለምናለን።  አሰላሙ አለይኩም ወራህመቱላሂ ወበረካቱ!

2 Responses to About us

  1. Nur adam says:

    I love your radio program I start listen not vary long ago I promise my self I will be your listener and supporter 

    I really satisfied the interview you have with imam Khalid( first Hijra imam) you are good you ask vary important qaostion about new organization that they shouldn't do They try so hard to colapce BADR Ethiopia 

    I don't know why they did that please keep ask hard ??? So we can or they can anderstand thanks keep it up 

  2. Mohammed Abdulwahab says:

    What is the next steps are you looking to do demtsachen yesema. Still waiting for dream answer from EPRDF. By peaceful like Muslim Brother hood or Gandy OR Dr.Mlk stile. It doesn’t work for Islam.Muslim struggle fellow the prophet Mohammed.

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *